የማንቂያው ደወል በደቡብ ሱዳን ተሰምቷል

የካቲት 17, 2009 (GCDC) - የግብጽ አየር ኃይል .. የካቲት 3 ቀን 2017 ከኢትዮጵያ ድንበር 200 እስክ 300 ኪሎሜትር ርቀት፣ ማካላ በሚባለው ቦታ ላይ በሚገኙ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን ተቃዋሚዎቹ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በወቅቱ ይህንን ዘገባ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዘግበውታል። ግብጽ ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ አህመድ አቡዚያድ በኩል፤ «ግብጽ በሌላ አገር ጉዳይ ጣልቃ አትገባም» ስትል ክሱን ውድቅ አድርጋለች፡፡ ደቡብ ሱዳን በበኩሏ፣ በደቡብ ሱዳን ግዛት ውስጥ ምንም አይነት የቦምብ ድብደባ አለመካሄዱን በማንሳት «ትርጉም የማይሰጥ ክስ» በማለት ክሱን አጣጥላዋለች።

ለኢትዮጵያ ቅርብ በሆነ አካባቢ በደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎቹ ላይ የተካሄደው የአየር ድብደባ በእርግጥ በግብጽ ስለመፈጸሙ መከራከሪያ ነጥቦችን በማሳየት፤ «ለኢትዮጵያ የማንቂያ ደወል ነው» ሲሉ የፀጥታና የፖለቲካ ምሁራን እያሳሰቡ ናቸው፡፡ መወሰድ ስላለበት ጥንቃቄና እርምጃም ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ሆነው የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ሲያማክሩ የነበሩትና በግጭትና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሚሰሩት አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ፣ በደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ላይ የተደረገው የቦንብ ድብደባ የግብጽ ስለመሆኑ ጥርጥር እንደሌለው ይገልጻሉ። «ከደቡብ ሱዳን መንግሥት የውስጥ አዋቂዎች መረጃ እንደሚያመለክተው የቦንብ ድብደባው የተካሄደው ዲዲዲ ሦስት አንቶኖቭ እና ሚግ 29 በተባሉ የጦር አውሮፕላኖች ነው። እነዚህ አውሮፕላኖች በአፍሪካ ያላቸው አገራት ደግሞ አልጀሪያና ግብጽ ብቻ ናቸው። አልጀሪያ በደቡብ ሱዳንም ሆነ በቀጣናው አገራት ምንም ዓይነት ፍላጎት ስለሌላት አውሮፕላኗን ልካ ድብደባ አታካሂድም፡፡ ስለዚህ ድብደባውን ከግብጽ ውጪ ማንም ሊፈጽመው አይችልም» ይላሉ።

እንደ አቶ ካህሳይ ገለጻም፤ ግብጽ ድብደባውን አካሂዳ በቀጥታ ወደ ግዛቷ መመለስ ስለማትችል የጦር አውሮፕላኗን በአንድ ቦታ አሳርፋለች። አብዛኛዎቹ የቀጣናው አገራት ደግሞ የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በግዛታቸው ውስጥ እንዲያርፉ አይፈቅዱም፡፡ ነገር ግን ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር ከፍተኛ የጥቅም ትስስር ያላትና ከግብጽ መንግሥት ጋር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወዳጅነቷ እየጨመረ የመጣው ዑጋንዳ ሳትፈቅድ አልቀረችም፡፡ ከደቡብ ሱዳን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የጦር ሄሊኮፕተር ማሳረፊያ ቦታ ያላት መሆኑ ደግሞ ግምቱን ይበልጥ ያጠናክረዋል፡፡

የቀድሞው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ በበኩላቸው፣ የአየር ድብደባው በጣም ከከፍታ ላይ የተፈጸመ ነው። ይህን ማድረግ የሚችል አገር ደግሞ ግብጽ ብቻ ነው የሚል ድምዳሜ አላቸው። ከድብደባው አስቀድሞ በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የፖለቲካ ንግግር መደረጉን ያስታውሱናም፣«ድብደባው የተካሄደው ለግብጽ ታዛዥ የሆነውን የፕሬዚዳንት ሳልቫኪር መንግሥትን ዕድሜ ለማራዘም የተደረገ ቢሆንም ለኢትዮጵያም ልዩ ትርጉም የሚሰጥ ነው» ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ አበበ አይነቴም ድብደባው በግብፅ ስለመፈጸሙ ጥርጥር እንደሌላቸው በመግለጽ ምክንያት ያሉትን ያስቀምጣሉ፡፡ ግብጽ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ለመቀበል ተቸግራለች። በመሆኑም በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና በኤርትራ ያለውን አለመረጋጋት ተጠቅማ ኢትዮጵያ ላይ ጉዳት የማድረስ ፍላጎት አላት።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ተስፋም ተመሳሳይ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ግብፆች ከግድቡ ጋር ያለው አቋማቸው ስላልበረደ ይሄንን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ የግብጽ የፀጥታ ኃይል በደቡብ ሱዳን መግባቱ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳና ግብጽ እየሄዱበት ያለው መንገድ፣ ግብጽ እና የግብጽ አጋሮች የሶማሊያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳን እና የጅቡቲ ወደቦችን በተለያየ መልኩ ለመቆጣጠር መሞከራቸው ኢትዮጵያና ሌሎች የቀጣናው አገራት በአካባቢው ሰላም ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያደናቅፍና ኢትዮጵያንም የሚያዳክም ነው፣ የዶክተሩ ስጋት ነው።

አቶ ካህሳይ እንደሚሉት ደግሞ፣ «ግብፆች ቀደም ሲል በምዕራባውያን ዘንድ የዓረቡ ዓለምና የመካከለኛው ምስራቅ ዋና መልዕክተኛና አማላጅ በመሆን ከአሜሪካ ብቻ በዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር ያገኙ ነበር። አሁን ቀርቷል፡፡ ይሄንን ዓይነት ሚና በአፍሪካ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፣ ይሄ ሚና ደግሞ በኢትዮጵያ እየተያዘ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን በማዳከም የበላይነቱን ማስጠበቅ ይፈልጋሉ። ለዚህ ምኞታቸው ስኬት ደግሞ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የላቸውም»

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ «ግብጽ አሁን እየሄደችበት ያለው አቅጣጫ፣ በደቡብ ሱዳንም የሚሸተው የባሩድ ጠረን ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው አገራት ጥሩ አይደለም። በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ ችላ ሳትል ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት፣ ለአውሮፓ ህብረት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት፣ ለኃያላን አገራት፣ ለእራሷ ለግብጽና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አገራት አጋሮቿ እየሄዱበት ያለው መንገድ ትክክል አለመሆኑን፣ እንደ አልሸባብ ያሉ አሸባሪዎችም እንዲያንሰራሩና ሌሎች እንዲፈጠሩ ስለሚያደርግ ማሳወቅና ማስረዳት አለባት» ሲሉ መክረዋል።

ጀኔራል ጻድቃንም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ባነሱት የዲፕሎማሲ አካሄድ ይስማማሉ፡፡ በተጨማሪነትም በደቡብ ሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ የማዶ ተመልካች መሆን ስለማይገባ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር ሥራ መሥራት ይገባል ይላሉ። «የአገራችንን ጥቅም ከሚያስከብርና አብሮ ከሚቀጥል አካል ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል። ይህን ግንኙነት የሚረብሹ ኃይሎችን ጠንካራ በሆነ አቋም እዚህ ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ማስረዳት ያስፈልጋል። ማስጠንቀቂያውን አልፈው ከገቡ ግን አጸፋውን ለመመለስ ዝግጁ መሆን ይገባል። የኢትዮጵያ የስለላ መዋቅር ጠንካራ ስለሆነ በአገር ውስጥ ችግር ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም ኡጋንዳም ሆነች ግብጽ ደቡብ ሱዳን ገብተው በሚፈተፍቱበት ወቅት እኛ ዝም ማለት የለብንም፡፡ ስለሆነም ያሉትን ክስተቶች እየተነተኑ ተስማሚ ስልት ነድፎ የሚቃጣውን አደጋ ማስቀረት የግድ ይላል» ሲሉ መክረዋል፡፡

አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ግብጽ የምትናገረውና የምትሰራው የተለያየ ነው። በኢትዮጵያ ላይ ችግር ለመፍጠር የምትጠቀምባቸው ጆከሮቿ ሶማሊያ፣ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን ናቸው። በእነዚህ አገራት በኩል የሚመጣውን ችግር ለመቋቋም የቀጣናውን የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቅ በማጥናት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር እራስን ዝግጁ በማድረግ በዲፕሎማሲና በፀጥታ በተጠንቀቅ መቆም ያስፈልጋል። በደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ላይ የተፈጸመው ድብደባም ለኢትዮጵያ የማንቂያ ደወል ነው ብለዋል፡፡ (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)