የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ስፍራዎች ባደረሱት ጥቃት 28 ሰዎችን ገድለው

አዲስ አበባ መጋቢት 5 2009 (GCDC) ለድንበር አዋሳኝ በሆኑ የጋምቤላ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር እየተሰራ ነው

ከመጋቢት አንድ እስከ ሶስት ባሉት ቀናት ውስጥ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ስፍራዎች ባደረሱት ጥቃት 18 ሰዎችን ገድለው ሌሎችን ማቁሰላቸው ተነግሯል።

ታጣቂዎቹ 43 ህጻናትን አግተው የወሰዱ ሲሆን የተወሰኑ መኖሪያ ጎጆዎችንም አቃጥለዋል። በጉዳዩ ላይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የመንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ችግሩ በተደጋጋሚ መፈጠሩን ጠቅሰው፥ ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም ባለፉት ሶስት ቀናት በአካባቢው ጥቃት ያደረሱ ታጣቂዎችን በመከታተል ህጻናቱን በማስመለስ እርምጃ ለመውሰድ መሰማራቱንም ነው የተናገሩት፤ የሚገኘው ውጤትም ይፋ እንደሚሆን በመጥቀስ።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከመሰረቱ ምክንያቶችን በመመርመር መንግስት አካባቢው በፀጥታ አካላት የሚጠበቅትን ሁኔታ እንዲሁም ሁለቱን ሃገራት በልማት ለማስተሳሰር ይሰራልም ብለዋል።

ከዚህ አንጻርም የተጀመሩ የመንገድ፣ ህዝቡን በመንደር የማሰባሰብ እንዲሁም ለህዝቡ ጥበቃ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት። ጥቃቱን ያደረሱት ታጣቂዎች የትኛውንም መንግስት አይወክሉም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ችግሩን ለመፍታት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በደቡብ ሱዳን በኩል አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በድንበር አካባቢ ያለው ጥበቃ እንዲጠናከር ቢደረግም አሁንም ችግሮች መከሰታቸውንም ነው የገለጹት።

ከዚህ አንጻር በደቡብ ሱዳን በኩል ከአመለካከት አንጻር ስራዎች እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እና የክልሉ ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ አንስተዋል። ትልቁ ጉዳይ አካባቢውን ማልማት በመሆኑና ችግሮች ሲፈጠሩም በቀላሉ መድረስ እንዲቻልም በአካባቢው መሰረተ ልማት መሟላት እንዳለበት ጠቅሰዋል። መንግስትም ለተፈጠረው ችግር አስፈላጊውን ምላሽ እየሰጠ ችግር ፈጣሪዎቹን ለህግ ያቀርባልም ብለዋል፤ በዘላቂነት ችግሩ እንዳይፈጠርና እንዳይደገም እንደሚሰራ በመጠቆም። (ኤፍ ሲ)