ጋህአዴን ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል፡፡

ጋምቤላ, መስከረም 18, 2010 (GCDC) - ባለፉት ዓመታት የጋምቤላን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፉ ብዙ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋህአዴን/ አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ጋትሉዋክ ቱት እንደገለጹት የክልሉ ህዝብ ቀደም  ሲል በነበሩት ስርዓቶች ተረስቶና አስተዋሽ አጥቶ የልማት ተጠቃሚ ሳይሆን  ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ በህዝቦች የጋራ ጥረት የአምባገነኑ ስርዓት ከተወገደበት ማግስት ጀምሮ በጋህአዴን መሪነት እራሱን በራስ በማስተዳደር ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ  የልማት ስራዎች እንደተከናወኑ ነው ሊቀመንበሩ ያስታወቁት፡፡

በተለይም  በመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም፣ በትምህርት በጤና በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በመንገድና በሌሎችም የመሰረተ ልማት ዘርፎች ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የመንደር ማሰባሰብ መረሃ ግብር የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የተጠናከር የኤክስቴንሽን አደረጃጀትና የግብአትን አቅርቦት በማጎልበት    አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ወደ ተሻለ የግብርና ልማት እንዲገባ መደረጉን አቶ ጋትሉዋክ ተናግረዋል።

ድርጅቱ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የህዝቦች ዋነኛ ፈተና እየሆነ የመጣውን የመልካም አስተዳደር ችግርን ለማስወገድ ባደረገው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ በርካታ ብልሹ አሰራሮችና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችን የማጥራት ስራ አከናውኗል ሊቀመንበሩ እንዳሉት።

በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት የጎሰኝነት፣የጠባብነትና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ባላቸው የውስጥና የውጪ ቡድኖች ህዝቡን በማጋጨት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍ ቢሞክሩም ማክሸፍ  መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ  ወቅት  በክልሉ የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም ተፈጥሮ ህዝቡ በተሻለ ሁኔታ ወደ ልማት ገብቷል።

"ጋህአዴን በቀጣይም የአባላቱን አደረጃጀት በማጠናከርና የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ቀጥለው ህዝቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል "ብለዋል አቶ ጋትሉዋክ

በድርጀቱ ጉባኤ ላይ የብአዴን የህወሐት፣ የኦህዴድ፣የደኢህዴንና ሌሎች የአጋር ድርጅት ተወካዮች በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት በመገኘት ለጋህአዴን ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

ጉባኤው በሶሰት ቀናት ቆይታው የድርጅቱን ያለፉት  ሁለት ዓመታት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና በቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ በመወያየት  እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

ድርጅቱን በቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚመሩ የማዕከላዊ ኮሚቴና የኦዲት ኮሚሽን ምርጫ እንደሚካሄድም እንዲሁ። (ኢዜአ)